
ግንቦት 10/2016ዓ.ም ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ
ጉራጌ ብዙ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ሲሆን የመንደር አመሰራረቱና ጀፎር የተሰኘው የባህላዊ የአውራ መንገድ ቅየሣ ወይም የምሕንድስና ጥበብ አንዱ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
“ጀፎር” ማለት የጉራጌኛ ቃል ሲሆን አውራ መንገድ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ይህ የ”ጀፎር” ፍልስፍና በጉራጌዎች መንደር የተጀመረው ገና በአገራችን ባለ አራት እግር የሞተር ተሽከርካሪዎች ሳይገቡና የመኪና ስሙ እንኳን በማይታወቅበት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደነበረ የጉራጌ አባቶች ይናገራሉ።
የጀፎር የጎኑ ስፋት ከ60-100 ሜትር እንደሚወስድ የሚገለጽ ሲሆን ርዝመቱ ግን አውራ መንገድ (ጀፎር) በሚያቋርጥባቸው አቅጣጫዎች ወንዝ፣ ደንና ትልልቅ ሸለቆዎች እስካላጋጠው ድረስ ቅያሱ ይቀጥላል፡፡ የመንገዱ ስፋት የሚለካውም በባህሉ መሠረት በተመረጡ አባቶች ወይም የመሬት ልኬት ዳኞች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጀፎር በሁለት መንደሮች ትይዩ በመካከላቸው አቋርጦ የሚያልፍና አረንጓዴ ሳር የለበሰ ውብና ጽዱ ባህላዊ አውራ መንገድ ነው።
ይህ በጉራጌ አባቶች ሀገር በቀል ዕውቀት የተጀመረው ባህላዊ የመንደር አመሠራረትና7 የአውራ መንገድ ቅየሣ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ትኩረት የሰጠና መሠረት ያደረገ መሆኑ ደግሞ የአባቶችን የአርቆ አሳቢነትና ጥልቅ የጥበብ ባለቤትነትን የሚያስረዳ ስለመሆኑ አይካድም።
ጀፎር መሃሉን አቋርጦ በሚያልፈበት ዳርና ዳር የሚታዩ መንደሮች በጉራጌዎች ጥበብ ተክነውና በሀገር በቀል ቁሳቁሶች የተሠሩ የጉራጌ ባህላዊ የጎጆ ቤቶች አይን የሚማርክ ገፅታ አላቸው።
ውብ የሆነው የባህላዊ አውራ መንገድ (ጀፎር) የአከባቢ ነዋሪዎች መግቢያና መውጫ ሆኖ ከማገልገል ባሻገር የተላያዩ ማህባራዊና ሀይማኖታዊ ኩነቶችን ለማካሄድ በጋራ የሚጠቀሙበት የወል ሥፍራም ነው፡፡
ሰፊ ስብሰባዎች ሲኖሩ የሚደረግበት፣ ባህላዊ የእርቅ ሥነ ስርዓት የሚከናወንበት፣ በመስቀል በዓል የደመራ ስነስርዓት የሚካድበት ነው፡፡ በሠርግ ጊዜም ሰርገኞች የሚጨፍሩበት፣ አባቶችና እናቶች ዘመድ አዝማድ ተሰባስበው ልጆቻቸውን መርቀው ለአማች የሚሰጡበት ቦታ መሆኑም ይነገርለታል፡፡ ሰው ቢሞት በሀዘን ጊዜም የለቅሶ ስነስርዓት የሚከናወነው በዚሁ ሥፍራ ነው፡፡
በተጨማሪም ሥፍራው የፈረስ ጉግስና የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች የሚካሄዱበት ሲሆን ለከብቶች መውጫና መግቢያ እንዲሁም ለመዋያነትም እንደሚያገለግል ይገለጻል።
ይህንን ውብ ሥፍራና በጎ ተሞክሮን ከማስተዋወቅና ለቱሪዝም መስህብ መዳረሻነት ከማዋል ረገድ የሚመለከተው አካል ድርሻውን ከተወጣ እነዚህን የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመንከባከብ በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቀም የጉራጌ ማህበረሰብ ማግኘት ይችላል።
መረጃው:- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ነዉ።
