ጥቅምት 1/2017 ዓ/ም [ወልቂጤ]


የጉራጊኛ ቋንቋ ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የጉራጊኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የፊደል ገበታና የትምህርት አሰጣጥ ላይ በተመለከተ በወልቂጤ ከተማ ለ2 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ቋንቋ ፦ባህልና እሴት ማሳደጊያ ፣ መግባቢያ ለትውልድ ማስተላለፊያ ቁልፍ መሳረያ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቋንቋ ማሳደግ የማንነት ጉዳይ ስለሆነ ቋንቋ የሌለው ህዝብ ደግሞ ማንነቱ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም ነው ያሉት።

ጉራጌ በርካታ ባህል ፣ ወግና ታሪክ ያለው ባህሉም ከራሱ አልፎ ለሌሎችም አራያ መሆን የቻለ ሲሆን ለአብነትም የቁጠባ እና የስራ ባህልን ተጠቃሽ መሆናቸው በንግግራቸው አንስተው እነዚህም እየተሸረሸሩ በመሆኑ በቀጣይ ጠብቆ ማቆየት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ከእነዚህ አንዱ የሆነው የጉራጊኛ ቋንቋ ከወደቀበት አንስቶ እንዲያሰራራ ለማድረግ በዞኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑ አቶ ላጫ ተናግረዋል።

አክለውም ለስራው አስፈላጊውን በጀት በመመደብ የጉራጊኛ መጽሀፍቶች የማሳተምና ስልጠናዎች መሰጠቱ ጠቁመው ከ 1 ሺ 2 መቶ በላይ የጉራጊኛ ቋንቋ መምህራንች መለየታቸው አብራርዋል።

ቋንቋው በተለያዩ ዘዮች የሚነገር ሲሆን ትምህርቱም ሲሰጥ በሁሉም ዘዮች ከተሰጠ በኋላ በቀጣይ ወደ አንድ የማምጣት ስራ እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን ቋንቋው ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ተቋሟት እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ እና የመምህራን ልማት ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር አቶ ባቂ በሰማ በበከላቸው ቋንቋ የሚለማው በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተቀርጾ ለዜጎች ትምህርት ሲሰጥበት፣የኪነ ጥበብ በሬድዮና በቴሌቪዥን ህዝብ ሲሰማው እና ሲገለገልበት ነው።

ይሁን እንጂ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርት እና የሚዲያ ቋንቋ ሳይደረገ በመቆየቱ ቋንቋው ተዳክሟል።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት ከቅድመ 1ኛ የተጀመረው ዛሬ ላይ የ2ኛ ክፍል የጉራጊኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጽሀፍ ዝግጅት ተጠናቆ የሙከራ ትግበራ ተጀምሯል ብለዋል።

አቶ ባቂ አያይዘውም በ2017 በ9 መቶ 31 ቅድመ አንደኛ ሙሉ የትምህርት አይነት፣በ4መቶ 3 1ኛ ክፍል እንደ አንድ የትምህርት አይነት ሙሉ ትግበራ እና በ2ኛ ክፍል በ18 ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ማስጀመር መቻሉ አስታውቀዋል።

ስልጠናውም ለመማሪያነት የተዘጋጁ የጉራጊኛ መጽሀፍቶች ከመምህራን እና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ለማስተዋወቅ እንዲሁም የመማር ማስተማሩ ስነ ዘዴ ላይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አመላክተዋል።

አቶ ባቂ አክለው በሁሉም ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችና በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጉራጊኛ ቋንቋ እንደሚሰጥም አመላክተዋል።


መረጃው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነው።