ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም


የክቡር ዶክተር ማሕሙድ አህመድ የመድረክ ሥራ የመጨረሻ ኮንሰርት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚኒሊየም አዳራሽ እደሚካሄድ አዘጋጆቹ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል።የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አስቻለው ሀይሌ በወቅቱ እንዳሉት የመድረክ ዝግጅቱን በደመቀ እና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለማካሄድ በቂ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በአገራችን ዘመናዊ ሙዚቃን ከባህላዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ጋር አዋህዶ በመዝፈን በአገራችን ገናና ስብእና የገነባው ዶ/ር ማህሙድ አህመድ 50 አመታት ለዘለቀው አገልግሎቱ አድናቂዎቹ እና ወዳጆቹ ኮሚቴ በማዋቀር ላለፉት ሁለት አመታት የተለያዩ ስራዋችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ይህንኑ በማስመልከት ዛሬ (አርብ ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም) በሸራተን አዲስ ሆቴል ኮሜቴው በሰጠው ጋዜጣዊ ላይ የጋሽ ማህሙድን የመጨረሻ የሙዚቃ መድረክ ማዘጋጀት፣ የጋሽ ማህሙድ የህይወት ታሪክ መጽሃፍ ህትመትና ምረቃ ማድረግ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራት በጋሽ ማህሙድ ስም መንገድ / አደባባይ ማሰየም፣ የጋሽ ማህሙድን ሃውልት ለማስቆም የሚያሰችል ስራዎችን መስራት ይገኙበታል።

ታላላቅ አርቲስቶች ህይወታቸው ካለፈ በኃላ መሰል ዝግጅት እንደሚካሄድ የገለጹት የኮሚቴው አባል አብረሃም ወልዴ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ሰው በህይወት እያለ ላበረከተው ተግባር ማመስገን አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፍ ስመጥር የሆነውን የሙዚቃ አባት ከሙዚቃ አለም ለመሰናበት ሲዘጋጅ እጅን አወዛውዞ ከመሸኘት ባለፈ ሽኝቱን በደመቀ እና በታሪክ ማስታወሻነት እንዲቀመጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

በኮንሰርቱ በአርቲስቱ የሙዚቃ ህይወት ታሪክ ላይ የተጻፈ መጽሃፍ እንደሚመረቅ፣ በአርቲስቱ ስም መንገድ መሰየምና ሃውልት ማቆም እንደሚገኝበት ተገልጿል።

በመጪው ጥር ወር ላይ በሚካሄደው ኮንሰርት ላይ 25 ሺህ ታዳሚያን ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

ጋሽ ማሕሙድ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጾ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

የዚህ የዜና ምንጭ የኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት ነዉ።