ሚያዝያ 22/2017 (ወልቂጤ)


ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ጉራጌ ዞንን መጎብኘታቸው ተገለፀ።

የጉራጌ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ እንዲሁም ተፈጥሯዊና ሰውሰራሽ ቅርሶች ለማስተዋወቅ አየተሰራ መሆኑ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በቱሪዝም፣ በባህልና በቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በጉራጊኛ ቋንቋ ዘርፎች በርካታ ስራዎች ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት በዞኑ የሚገኙ በርካታ የቱሪዝም ፀጋዎች በተለይም መስቀል በጉራጌ፣ የአብሬት መውሊድ፣ ኩርፍወ፣ ጀፎረ፣ የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ፣ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎችን ጨምሮ ሌሎች ገዳማት፣ ጥብቅ ደኖች ፣ ፍልውሃዎች፣ ሀይቆች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ማስተዋወቅና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በመሆኑም በበጀት አመቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ዞኑን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መሰረተ ልማት በማሟላት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ብሄር በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ መሰረት ቅርሶቹ በዘላቂነት ተጠብቀው እንዲቆዩ፣ እንዲተዋወቁ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑ አውስተዋል።

በዚህም ክትፎ፣ ወኸምያ፣ ጀፎረ እና ሌሎችም የሚገኙበት ሲሆን በቅርሶቹ ላይ ልዩልዩ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል።

የገጠር ኮሪደር አብነት የሆነው ጀፎረ ታሪካዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ለማስዋብ እየተሰራ ሲሆን ከ290 ኪሎ ሜትር በላይ ጀፎሮዎች ለማስዋብ፣ ለመጠበቅና የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ለማሰጠት እየተሰራ ነው።

የጉራጌ ባህላዊ እሴቶች እንደ እድር፣ እቁብ፣ ውጆ፣ ደማዳ የመሳሰሉትን ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎባቸዋል ብለዋል።

በየመዋቅሮቹ የጉራጌ የባህል ቤት እንዲገነቡ እና በነባርና አዳዲስ የባህላዊ ቁሳቁሶች እንዲደራጁና እንዲሟሉ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ከግብ ማድረስ ይገባል ብለዋል።

የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ቢኖሩም በቀጣይ ቋንቋው የስራ ቋንቋ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የተለያዩ ደራሲያን ጉራጊኛን በመጠቀም የስነጽሁፍ ስራዎች ለመስራት ያላቸው ተነሳሽነት እያደገ መሆኑንም አውስተዋል።

በዞኑ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በማጠናከር እና በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ ለማድረግ ለተቋማቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

ምንጭ: ጉ/ዞ/ኮ