
በመስቃን ቤተ-ጉራጌ በአረፋ በዓል ከሚከናወኑ ዋና ዋና ክዋኔዎች ውስጥ አንዱ የአዳብና ፌስቲቫል አከባበር ስነ-ስርዓት ተጠቃሽ ነው። የጉራጌ ባህል የሆነዉ የአዳብና ስነ-ስርዓት ዘንድሮ የጉራጌ ድምቀት በሆነዉ የመስቃን ጉራጌ ወረዳ በድምቀት ተከብሯል። የመስቃን ወረዳ ኮምንኬሽ ቢሮ ስለ አዳብና እና ስለ አከባበሩ የሚከተለዉን ዘገባ አቅርቧል።
አዳብና በወንዶችና በልጃገረዶች የሚካሄድ ሲሆን የአረፋን በዓል በማስመልከት የሚከናወን ደማቅ ፌስቲቫልም ነው።
አዳብና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አሉት፤ ማህበራዊ ጠቀሜታው መካከልም ፌስቲቫሉ ላይ ታዳሚዎቹ እርስ በርስ በሚያደርጉት የጭፈራ መስተጋብር አንድነትን ያሳያል እንዲሁም ይተጫጫሉ፤
በዚህ የተጀመረው የመተጫጨት ቅርርብ ባህልና ስርዓቱን ጠብቆ የቀጣይ ዘመን ውብ ተቋም ትዳር ይመሰረትበታል፤
የመተጫጨት ስርዓቱ አዳብና ላይ ቢጀመርም የሚጠናቀቀው ደግሞ ባህሉን ጠብቆ ቤተሰብ ጋር ደርሶም ነው።
ስለሆነም አዳብናው ላይ በዋናነት የሚሳተፉት ከስድስት ወር በፊት አግብተው ወደ አዳብና ስፍራ የመጡ ( ዥቧረ)፤ የታጬ ሴቶች( ቅፏፉኧ) ፣ ያጩ ወንዶች ( ወዳቡኧ) እና ወጣት ወንዶች(አርዴ) እና ልጃገረዶች ( አፍቶ) ናቸው።
አረፋና አዳብና ልዩ ግጥምጥሞሽ ያላቸው አስኪመስልም በፌስቲቫሉ አክባሪዎች ዘንድ ታላቅ ደስታና ፌሽታ ከመፍጠሩም በላይ በጉጉትና በናፍቆት እንዲጠብቁትም ያደርጋል፤ ተግባሩም የአዳብና ማህበራዊ ፋይዳ ማሳያ ነው።
በተጨማሪም አዳብና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፤ የፌስቲቫሉ ታዳሚዎች በሚጫወቱበትና በሚዝናኑበት ወቅትም ለመዝናኛና ለስጦታ ብለው ከረሜላ፣ማስቲካ፣ሉሚ፣ብርቱኳን እና መሰል ነገሮች በመሸጥና በመግዛት የገንዘብ ልውውጥ ያካሄዳሉ፤
ባህሉን የጠበቀ የአልባሳት፣ የጌጣጌጥና ሌሎች ነገሮችም ግዢ ይፈፅማሉ።
በመሆኑም አዳብና ባህልና ስርዓቱን ጠብቆ ማስቀጠል ሲቻል እነዚህና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ በዘመናዊነት እንዳይበረዝም ልዩ ጥበቃና እንክብካቤም ይፈልጋል።
አዳብና አረፋ በዓል ላይ የሚከበረው ከበዓሉ ማግስት ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት ሲሆን፤ ያገቡ (ዥቧረ)፣ የታጩ ሴቶችና ወንዶች ( ቅፏፉኧ ና ወዳቡኧ) እና ወጣት ወንድና ሴት ( አርዴና አፍቶ) አንድ ላይ ሆነው በተወሰኑ አካባቢዎች እየተዟዟሩ የሚያከናዉኑትም ነው።
መረጃው የምስራቅ ጉራጌ ዞን የመስቃን ወረዳ ኮምንኬሽን ነዉ።
