
ጉመር ወረዳ ከጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ በስተምዕራብ 65 km ከሀገሪቱ በደቡብ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 220 km ርቆ ይገኛል።
ወረዳው በ18 የገጠር ቀበሌዎች እና በ2 የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች (ቦሌ እና ባድ) የተዋቀረ ሲሆን የወረዳው ዋና ከተማ የሆነው አረቅጥ ከተማ ወደ ከተማ አስተዳደርነት አድጓል።
ጉመር ወረዳ በሰሜን እዣ ወረዳ÷ በደቡብ ጌታ ወረዳ÷ በምስራቅ ስልጤ ዞን እንዲሁም በምዕራብ ቸሀ ወረዳ ያዋስኑታል።
ወረዳው 233 ካሬ ኪ.ሜ የቆዳ ሥፋት ያለው ሲሆን ከባህር ወለል በላይ ከፍታው ከ2500 እስከ 3260 ሜትር የሚደርስ እና ሙሉ በሙሉ ደጋ የሆነ የአየር ሁኔታ ያለው ወረዳ ነው።
በተጨማሪም በወረዳው 3 ሀይቆች የሚገኙ ሲሆን አረቅጥ፣ የቦባ እና ደወሼ ሀይቆች በመባል ይታወቃሉ። በእነዚህ ሃይቆች እና በተለያዩ ቀበሌዎች በተሰሩ ኩሬዎች ላይ የአሳ ጫጬት በመጨመር አሳ በማምረት ለገበያ ማቅረብ ከተጀመረ ሰነባብቷል።
በወረዳች እና በአረቅጥ ከተማ አስተዳደር በድምሩ አንድ ኮንስትራክሽና ኢንድስትሪያል ኮሌጅ÷ አምስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች÷ 34 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች÷ አምስት ጤና ጣቢያዎች÷ አንድ ቀይ መስቀል መድሃኒት ቤት እንዲሁም አምስት የመብራት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ይገኛል።
ጉመር ወረዳ ለግብርና ምቹ የሆነ የአየር ሁኔታ እና መልካም ምድር ያለው ሲሆን በሰብል ልማት ገብስ፣ ባቄላ፣ አተር በስፋት ይመረታል። ስንዴ በመኸር እና በበጋ መስኖ በስፋት ማምረትም ተጀምሯል።
በእንስሳት ዘርፍም ለከብት እርባታ፣ ለበግ እርባታ፣ ለዶሮ እርባታ፣ ለንብ ማነብ፣ ለአሳ ማስገር የተመቸ ነው።
በአትክልትና ፍራፍሬ ፖም፣ ፕሪም፣ ድንች፣ ካሮት፣ የሃበሻ ጎመን የመሳሰሉት በስፋት ይመረታል።
በወረዳው ስድስት ከተሞች ተመስርተው ወረዳው ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል።
የወረዳው ዋና ከተማ የሆነው አረቅጥ ከተማ ወደ ከተማ አስተዳደር በማሳደግ በአራቱም አቅጣጫ እንዲሰፋ በማድረግ ሙሉ መዋቅር ተቋቁሞ ከንቲባ ተሰይሞለት ሥራ ከጀመረ አመታት አስቆጥሮዋል። እስካሁን በሆቴል፣ በሎጅ እና የዱቄት ፋብሪካ አቋቁሞ ለመሥራት ለባለሀብቶች ቦታ ተሰጥቷቸዉ ወደስራ ገብተዋል።
ቦሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በአራቱም አቅጣጫ እንዲሰፋ ተደርጎ ማዞሪያም የቦሌ አካል እንዲሆን በማድረግ የትስስር ፕላን ተሰርቶ ፀድቋል።
የወረዳው ተወላጅ ባለሀብቶች ወደ ከተማው መጥተው እንዲያለሙ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት የወረዳው መንግሥት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ባድ ማዘጋጃ ቤት በአራቱም አቅጣጫ እንዲሰፋ ተደርጓል። በቀጣይም የትስስር ፕላን ይሰራለታል። ከተማው መብራት ያለው፣ በክልል ገጠር መንገድ የታቀፈ ወደ አረቅጥ እና እምድብር የሚወስድ መንገድ ያለው፣ ጤና ጣቢያ፣ ሃይስኩል እና ጁንየር ትምህርት ቤት ያለው ነው።
ጀንቦሮ ከተማ ወደ ማዘጋጃ ቤት ከፍ ብሏል።
አበጃይ እና ዚዘንቾ ከተሞች ወደ ማዘጋጃ ከተማ ለማሳደግ በእቅድ ከተያዙ ከተሞች ውስጥ ናቸው።
ባለሀብቶች እና የአካባቢው ተወላጆች በወረዳው በሚገኙ ከተሞች በኢንዱስትሪ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢንቨስት እንድታደርጉ የወረዳው አስተዳደር ጥሪ አቅርቧል።
ምንጭ: በጉራጌ ዞን የጉመር ወረዳ ኮምንኬሽን ቢሮ።

